Friday, December 13, 2019

ከእኔ የተሻሉ



በአገራችን ተደማጭ የሆነው የሸገር ጨዋታ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መአዛ ያለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 3ዐ/ 2ዐዐ8 አርቲስት ሀመልማልን እንግዳ አድርጋ አቅርባት ነበር፡፡
ለሀመልማል እናቷን በተመለከተ ከመአዛ ለቀረበላት ጥያቄ ምላሽ እየሰጠች እንዲህ አለች እናቴ ለእኔ እሷ ያለገኝችውን ነገር ሁሉ ለእኔ አድርጋልኛለች፣ የእሷን ፍላጎት ትታ የእኔን ለማሟላት ለፍታለች፤ እኔም ራሴን ከቻልኩ በኋላ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ለማድረግ ጥሬያለሁ፡፡ እናቴ ለእኔ እንደሆነችው ሁሉ እኔም ለልጆቼ ከእኔ የተሻለ ነገር እንዲያገኙ ከእኔ የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ለፍቻለሁ አለች ፡፡

ይህ በአብዛኛው እናቶች ዘንድ እውነት የሆነ ነው፡፡ እናቶቻችን እነሱ መማር እየፈለጉ እኛን ሲያስተምሩ፣ እነሱ መልበስ እያማራቸው እኛን ሲለብሱ፣ እነሱ እያራበቸው እኛን ሲያጠግቡ፣ እኛን ከፍ ከፍ እያደረጉ እነሱ ግን ዝቅ ቅዝ ሲሉ አይተናል፡፡
እኛስ የአሁን ዘመን እናቶች በእውነት ይህን መስዋእትነት ለልጆቻችን ለመክፈል ዝግጁዎች ነን?
እኔ በበኩሌ እናቴ እንዴት አድርጋ አምስት ልጅ ሲደመር የሙሉ ቀን አስተማሪነትን ይዛ እዚህ እንደደረሰች እና እኛንም እዚህ እንዳደረሰች ሳስብ በን ምትሀት ነው እላለሁ፡፡ በዚህ አጭር የእናትነት ጊዜዬ የተማረርኩባቸው፣ የደከምኩባቸው፣ ያዘንኩባቸው፣ ተስፋ የቆረጥኩባቸው ቀናቶች ብዙ ናቸው፡፡ ልጆቼን ያማረርኩበትም ቀን እንደዛው፡፡

የእናቶቻችንን ጥንካሬ፣ ቆራጥነት፣ ተስፋ፣ አላማ፣ ብርታት፣ እምነት፣ ቻይነት፣ እና ትንሽ አምላክነት ይኖረን ዘንድ ለእኛ ለዚህ ትውልድ እናቶች እመኛለሁ፡፡

እናቶቻች እኛን ከእነሱ እንድንሻል አድርገው አሳድገውናል፣ እኛም ልጆቻችን ከእኛ የበለጡ አድርገን የማሳደግ ግዴታ አለብን፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን የትውልዱ ክስረት በእኛ ራስ ላይ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ይርዳን

/ሮዝ መስቲካ/

No comments:

Post a Comment