Friday, December 13, 2019

ሮዝ መስቲካ፡ 'ተጨማሪ የወሊድ ፈቃድ ለእናቶች' ስትል የምትወተውተዋ እናት (ቢቢሲ)

ሮዝ መስቲካ፡ 'ተጨማሪ የወሊድ ፈቃድ ለእናቶች' ስትል የምትወተውተዋ እናት


ሮዝ ከልጇ ጋርImage copyrightROSE MESTIKA

ዓለም አቀፍ የጡት ማጥባት ሳምንት በኢትዮጵያ ለ11ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው። የእናት ጡት ወተት ለልጆች ጤናማ አካላዊና አዕምሯዊ እድገት ወሳኝና መተኪያ የሌለው ነው። ለዚህም ነው እናቶች ልጆቻቸውን ያለ ተጨማሪ ምግብ እስከ ስድስት ወር ድረስ ከዚያም ከተጨማሪ ምግብ ጋር እስከ ሁለት ዓመት ድረስ እንዲያጠቡ የሚመከረው።
ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ይህንን መተግበር አዳጋች ሲሆን ይስተዋላል።
ልጆችን ጡት ማጥባት ሳይንስ ነው። ከእናትየዋ አመጋገብ ጀምሮ (የምግብ አሠራር በሉት) ቀላል አይደለም። አቀማመጡ፣ የልጅ አስተቃቀፉ፣ የጡት አጎራረሱ በዘፈቀደ የሚደረግ አይደለም።
መራመድ ቢፈልጉም ለረዥም ሰዓት ለመቀመጥ ይገደዳሉ። እጅ ይዝላል። ፍላጎት ባይኖርም መመገብ ይጠይቃል፤ ያገኙትን አሊያም ያሻዎትን ሳይሆን የተመጣጠነ ምግብ። አጣደፊ ጉዳይ ቢገጥመዎት ጡትዎን ከልጅዎ አፍ መንጠቅ ያሳሳል። ግራኝ ሆኑም ቀኝ በሁለቱም ክንድዎ ልጅዎን ማቀፍ ግድ ይላል- ሁለቱንም ጡቶች ማጥባት ስላለብዎ።
ያስርባል፤ ልብ ያዝላል። ያጠቡትን የጡት ወተት መጠንን የመስፈሪያ መንገድ ስለሌለ ልጅዎ ምን ያህል የጡት ወተት እንዳገኘ በቀላሉ ለማወቅ ስለማይቻል ያስጨንቃል።
ለእናት ከባዱ ነገር ደግሞ ልጀ አልጠገበም ብሎ ማሰብ ነው። አንዳንዴም የጠቡት ይወጣና ለንዴት ይዳርግዎት ይሆናል። ወተት አግቷል አላጋተም ጡትዎን የሚዳብሱበት ቁጥር ይበረክታል።
ጠብተው ሲጨርሱም ቆሞ ማስገሳት አለ። በተለይ ለጀማሪ እናቶች አሳሩ ብዙ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ የትዳር አጋሮች ድርሻቸውን ካልተወጡ ፈተናው ያይላል- ጡት ወደ ማስጣል ውሳኔም ሊያደርስ ይችላል። ይህን ያለችን ሮዝ መስቲካ ናት።
በማስ ኮሚዩኒኬሽን የመጀመሪያ ድግሪ አላት። በተለያዩ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግላለች። በሚዲያው ዘርፍም በጋዜጦችና በራዲዮ ፕሮግራሞች ላይ ሠርታለች።
'ሁለት ሦስት መልክ - ልጅ ወልዶ ማሳደግ' የሚል መፅሐፍ አላት። መጽሐፉ ከእርግዝና ጀምሮ ልጆችን በማሳደግ ሂደት የገጠሟትን ፈተናዎች እና የሌሎች እናቶች ተሞክሮ ተካቶበታል።
ሮዝ መስቲካ 'ተጨማሪ የወሊድ ፈቃድ ለእናቶች' በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች በምታደርገው ዘመቻዎቿና ቅስቀሳዎቿ ትታወቃለች።
ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ናት።
ከመጀመሪያ ልጇ በስተቀር ሦስቱን ልጆቿን ለተከታታይ ስድስት ወራት ያለተጨማሪ ምግብ አጥብታለች።
የመጀመሪያ ልጇን ስትወልድ በልምድ ከምታውቀው ውጪ የተሻለ ግንዛቤ ስላልነበራት እና የወለደችበት የጤና ተቋም ልጇ እንደተወለደ እንገር በመስጠት ፋንታ የዱቄት ወተት ስለሰጡት ጡት መጥባት አሻፈረኝ ብሎ እንደቀረ ምክንያቱን ትናገራለች።
እግረ መንገዷን ኃላፊነታቸውን በሚገባ የማይወጡ የጤና ተቋማትን በመኮነን ነው ታዲያ።
በዚህ ጡት ባልጠባው ልጇና በሌሎቹ መካከል በሽታን በመቋቋም ረገድ ልዩነቱ ከፍተኛ መሆኑን አስተውላለች። እርሱ በቀላሉ በጉንፋንም ሆነ በትንሽ በሽታ ይዳከማል፤ ሌሎቹ ግን በሽታን የመቋቋም አቅማቸው የተሻለ ነው።
በወሬ መሃል ሳይጠባ ማደጉን ሲሰማም 'ለምን?' ብሎ ይጠይቃታል፤ ይናደዳል። እርሷም በእርሱ ፊት እንዲህ ብላ ማውራት ትታለች።
ሮዝ፤ ልጆቿን እንደ እርሷ ሆኖ የሚንከባከብ ሰው ስለሌለ የመጀመሪያ ልጇን እንደወለደች ከባለቤቷ ጋር ተማክራ ሥራዋን ትታ ልጆቿን በማሳደግ ተጠምዳ ትውላለች። ምን አልባት አማራጮች ቢኖሩ፣ የወሊድ ፈቃድ ጊዜው ቢጨመር፣ ሥራ ቦታዎች የሕፃናት ማቆያ ቢኖር ወደ ሥራዋ ተመልሳ መድረስ የምትፈልግበት ቦታ ልትደርስ ትችል እንደነበር ታስባለች።

ሮዝ ልጇን ስታጠባImage copyrightROSE MESTIKA

ልክ እንደሷ ሁሉ አገራቸው የምትፈልጋቸው፣ ችሎታና አቅም ያላቸው ሴቶች እየተቆጩ በየቤታቸው ቀርተዋል ትላለች። ሩቅ ሳትሄድ እናቷ እርሷን ለማሳደግ ሲሉ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን ዋቢ ታደርጋለች።
"ከልጅነቴ ጀምሮ የሴቶች ኑሮ በጣም ያሳዝነኛል፤ ያሳስበኛል። እናቴ መምህር ስለነበረች የከፈለችውን ዋጋ አውቃለሁ። ቀኑን ሙሉ ታስተምራለች፤ ቤት ውስጥ ደግሞ ሙሉ ጊዜዋን በቤት ውስጥ ኃላፊነቶች ተወጥራ ትውላለች። በዚህም ሴቶች ያሉባቸውን ችግሮች እያየሁ ነው ያደኩት" ትላለች።
በዚህም ተነሳስታ በ1996 ዓ.ም የሴቶች ጉዳይ ላይ ብቻ የሚያተኩር 'አብነት' የተባለ መጽሔት ጀምራ ነበር።
እርሷ እንደምትለው በቂ ዝግጅት ሳታደርግ በመጀመሯና ገበያ ላይ የሚፈለገው ይዘት ታዋቂ ሰዎች ላይ ያተኮረ፣ ስሜታዊነት የሚንፀባረቅበት፣ የሴቶች ሕይወት ላይ ሳይሆን አካላዊ ቁንጅና ላይ ያተኮረ ስለነበር ገበያ ላይ እምብዛም አልቆየም።
ሴቶች ላይ የሚሰሩ ተቋማትም እንደዚህ ዓይነት ሥራዎችን የማበረታታትና የመደገፍ ልምዱ የላቸውም።
ያኔ ነው ስለሴቶች አብዝታ መቆርቆር የጀመረችው።
"ከባለቤቴ ድጋፍ በማግኘቴና ሥራዬን ለቅቄ ልጆቼን ማጥባት የቻልኩት እድለኛ ሆኜ ነው፤ ይህ እድል የሌላቸው እናቶችስ?" ጥያቄዋ ነው።
"ትዳር መያዝና ልጅ መውለድ ስኬታማነት እንደሆነ በማሰብ፤ ወግ ማዕረጉን እንጂ በውስጡ ያለውን ተግዳሮት በቀናነት የሚያካፍል የለም" ትላለች።
ሮዝ እንደምትለው የትዳር አጋር ጥሩ የገቢ ምንጭ ኖሮት ሥራ ትቶ ልጅ ማሳደግን መታደልና ደስታ ብቻ እንደሆነ ይቆጠራል። ይሁን እንጂ ሥራ ትቶ ልጆችን ማሳደግ ቀላል አይደለም። በአንድ ወቅት ድብርት ውስጥ ገብታ እንደነበር ታስታውሳለች - ሮዝ።
ምንም እንኳን ባለቤቷ ድርሻውን በመወጣቱ ፈተናዎቹን ማለፍ ብትችልም፤ ሥራ ትቶ ቤት ውስጥ መዋል በራሱ የሚያመጣውን ተፅእኖ እንዳለ በተግባር ተመልክታዋለች። ይህ በሌለበት ግን ቤተሰባዊና ማህበራዊ ቀውሶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ትናገራለች።
እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ዘመቻ ወደ ማካሄዱ እንዳዘነበለች ትናገራለች - ሮዝ መስቲካ።
እንዲህ ዓይነት ዘመቻዎችን ማካሄድ ከጀመረች አራት ዓመታትን አስቆጥራለች። በባለቤቷ ሥራ ምክንያት ወደ ህንድ አገር ተዛውረው ሳለ እዚያው ሆና ነው የጀመረችው። በማህበራዊ ሚዲያዎች በምታካሂዳቸው ዘመቻዎች እናቶች ተጨማሪ የወሊድ ፈቃድ እንዲያገኙና ያለ ተጨማሪ ምግብ ልጆቻቸውን ጡት እንዲያጠቡ ቅስቀሳዎችን ታደርጋለች።
ሮዝ ሐምሌ 27/2011 ዓ.ም የጡት ማጥባት ሳምንትን በማስመልከት በጁፒተር ሆቴል መሰናዶ አዘጋጅታለች። በዝግጅቱ ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርባሉ፤ ለስድስት ወር ያህል ያለተጨማሪ ምግብ፤ ከስድስት ወር በኋላ ለሁለት ዓመታት ልጆቻቸውን ያጠቡ እናቶችን ይበረታታሉ። የሕፃናት ማቆያ ያላቸው መሥሪያ ቤቶች ይመሰገናሉ።
የግል ድርጅቶች ሆነው መንግሥት ከሚፈቅደው ውጪ የወሊድ ፈቃድ የጨመሩ ድርጅቶችም ምስጋና እንደሚቀርብላቸው ገልጻልናለች።

የሮዝ ያልተመለሱ ጥያቄዎች

ሴቶችንና ሕፃናትን የተመለከቱ ሕጎችን በዝርዝር ባትመለከተም የሚከተሉት ግን አሁንም ጥያቄዎቿ ናቸው።
• የወንዶች አጋርነት
• የወሊድ ፈቃድ የተከለከሉ እናቶች፤ እረፍት ወስደው ሲመለሱ ሥራቸውን ያጡ እናቶች ጉዳይ
• የህፃናት ማቆያ በየመሥሪያ ቤቱ እንዲቋቋም የሚያዘውን አዋጅ ትግበራ ክትትል
• እናቶች ልጆቻቸውን እስከ ስድስት ወር እንዲያጠቡ ለማድረግ ተጨማሪ የወሊድ ፈቃድ እንዲሰጣቸው የሚሉ
"ሁሉም ያሉት ፖሊሲዎች የሚተገበሩት ጤናማ ትውልድ ሲኖር ነው" የምትለው ሮዝ እናቶችና ሕፃናትን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች ጠንካራ መሆን እንዳለባቸው ታሳስባለች።

No comments:

Post a Comment