ብርቱ ሴት

ልጅ በመውለዷ ብቻ ማንም ሴት

 ወደ ኋላ አትቅር!

በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው የነበሩ ሴቶች፤ መምህራን፣ ጋዜጠኞች፣ ፀሐፊ፣ አስተዳዳሪ የጤና፣ የስነ ልቦና፣ የሂሳብ ስራ ባለሙያ፣ ዘርዝሬ በማልጨርሳቸው ሙያዎች ላይ የነበሩ ሴቶች በልጅ መውለድ ምክንያት ከስራቸው እና ከትምህርታቸው ይስተጓጎላሉ፡፡ ለቤተሰባቸው እና ለሀገራቸው ያበረክቱት የነበረው ነገርም ይገደባል፡፡ ከሁሉ በላይ ሴቲቱ የነበራት ህልም ለራሷ ልታሳካው ያሳበችው ግብ ያቆማል፡፡ “እንዲህ መሆን እፈልጋለሁ” ብላ የተመኘችው ነገር ሁሉ በጅምሩ ይቀራል፡፡ ለምን? ልጅ መውለድ ይህን የእሷን ምኞት እና ፍላጎት ማስቀረት አለበት? አንዲት አገር እናቶችን ቤት በማስቀመጥ በወንዶች እና በጥቂት ሴቶች ስራ ብቻ ማደግ ትችላለችን? ኑሮ እንዲህ እለት ተእለት በተወደደበት በዚህ ጊዜ በአንድ አባወራ ደመወዝ ብቻ ለልጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማሟላት ይችላል? ለሁሉም ጥያቄዎች መልሱ አይቻልም ነው፡፡

ስለዚህ ምን ይደረግ? ሰው እንዳአቅሙ ነውና፤ አገራችን የሞላት የደላት ባትሆንም ቅሉ እንደአቅሟ ለነዚህ እናቶች የድርሻዋን መወጣት ይኖርባታል፡፡ በአሁን ወቅት በስራ ገበታ ላይ ያለች ሴት የምታገኘው የወሊድ ፈቃድ በግል ድርጅቶች ሶስት ወር በመንግስት መስሪያ ቤቶች ደግሞ አራት ወር ነው፡፡

ይህ ሶስት ወይም አራት ወር ለእናትየውም ሆነ ለጨቅላው በቂ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የወሊድ ፈቃድ ወደ ስድስት ወር እንዲራዘም እና ደመወዟን እያገኘች ህፃኑን ስድስት ወር እስኪሆነው ድረስ በህክምና ባለሙያዎች እንደታዘዘው ጡት እንድታጠባው እና እሷም በደንብ ሰውነቷ እስኪጠገን በቤቷ እንደትቆይ የሚያስችላትን ፈቃድ ማግኘት አለባት፡፡ ይህ ለጤናማ ህፃንና ለጤናማ እናት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ጤናማ ህፃን ማሳደግ ማለት ጤናማ ትውልድ መተካት ማለት ነው፡፡ የእናት ጤና ማጣት፤ የስነልቦና እና የአካላዊ ጤና መጓደል በአንድ ቤተሰብም ሆነ በአገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

“የውሀ ጠብታ እያደር ድንጋይ ይበሳል” እንደሚባለው ይህ የወሊድ ፈቃድ አንድ የውሀ ጠብታ ሆኖ የእናቶችን፣ የቤተሰብን እንዲሁም የአገርን ደረጃ ያሻሽላል፡፡
ይህንን እንቅስቃሴ እውን ለማድረግ እና ግንዛቤ ለመፍጠር የተከፈተውን “ተጨማሪ የወሊድ ፈቃድ ለእናቶች” የሚለው ገፅ ደጋፊዎች በመሆን ገፁንም ለሌሎች ወዳጆቻችሁ በማካፈል እንዲሁም ገፁን እንዲመለከቱት በመጋበዝ ሀሳባችንን እንዲሳካ ታግዙን ዘንድ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡
እስካሁን ድረስ ይህን ሀሳብ በመደገፍ እና ገፁን በማካፈል ሌሎች እንዲያውቁት ላደረጋችሁ ሁሉ ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡

ሮዝ መስቲካከእናቶቹ አንዷ

No comments:

Post a Comment